አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህርዳር-ጎንደር ኮማንድ ፖስት በጽንፈኛው ቡድን ላይ እየወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ቀጣናውን ሠላማዊና የተረጋጋ ማድረግ ተችሏል ሲሉ የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ ገለጹ፡፡
ኮማንድ ፖስቱ የቀጣናውን አሁናዊ ሁኔታና የዕቅድ አፈፃፀም መነሻ በማድረግ ከኮር አመራሮች፣ ከዞን መስተዳድርና ከፀጥታ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ ግምገማ አካሂዷል፡፡
ሌ/ጄ ብርሃኑ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አሁናዊ የቀጣናው ሁኔታ መሻሻል እያሳየ ነው፤ ህብረተሰቡም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው በመመለስ የተረጋጋ ሕይወቱን መምራት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ በጽንፈኛው ቡድን ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉ ገልጸው፤ የክልሉን ሠላም በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ሠራዊቱ ግዳጁን በላቀ ጀግንነት እየፈፀመ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የሠራዊቱን ምት መቋቋም ተስኖት ተበታትኖ በመንደርና በየጫካው የተሰገሰገውን ቡድን በአጭር ጊዜ በመደምሰስ ለአርሶ አደሩ የግብርና ስራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡
የአካባቢውን ማህበረሰብና የፀጥታ መዋቅሩን አቅም በመጠቀም ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባም ማሳሰባቸውንን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡