አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሽፋን 91 በመቶ መድረሱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዘርፉን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃጸም እየገመገመ ነው፡፡
አቶ ገብረመስቀል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የንግዱን ማህበረሰብ ፍትሃዊ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ተግባራዊ የተደረገው ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሽፋን 91 ደርሷል፡፡
አገልግሎቱ የንግዱን ማህበረሰብ እንግልት፣ የጊዜና የገንዘብ ወጪ ከመቀነሱም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የንግድ ሥራን ለመጀመር ያላትን ምቹነት ለማሻሻል ያስችላል ብለዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሚሊየን 849 ሺህ 260 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን በኦን ላይን መስጠት መቻሉንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡