አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐሰተኛ የመጀመሪያ ዲግሪና የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎችን ተጠቅሞ ሥራ የተቀጠረው ግለሰብ በሠባት ዓመት ጽኑ እስራትና 10 ሺህ ብር ተቀጣ።
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የኦሮሚያ ክልል የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የሻንቡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።
የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሆሮ ጉድሩ ዞን ሻንቡ ከተማ ምድብ ዐቃቤ ሕግ÷ ፍቃዱ ጋርቢቺ የተባለ ግለሰብ የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር (2) ሥር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፉን ጠቅሶ ክስ መስርቶበታል።
በቀረበው ክስ ላይም ተከሳሹ፥ በሻምቡ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረ በማስመሰል የ11ኛ ክፍል እና የ12ኛ ክፍል ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እና ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠ የሚመስል የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃ እንዲሁም ሐሰተኛ የድጋፍ ደብዳቤ በማውጣት ከቪዥን ፈንድ ማይክሮ ፋይናንስ ማኅበር ሻምቡ ቅርንጫፍ 60 ሺህ ብር ብድር መቀበሉ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በመከላከያ ሰራዊት ለሥምንት ዓመት የሥራ ልምድ እንዳለው እና የመቶ አለቃ ማዕረግ እንዳለው የሚጠቅስ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በሻምቡ ከተማ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ቅጥር መፈጸሙ በክሱ ተጠቅሷል።
ተከሳሹ በዚህ መልኩ የቀረበበት ክስ ዝርዝር ከደረሰው በኋላ ወንጀል አለመፈጸሙን ጠቅሶ መከራከሩን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦበታል።
ፍርድ ቤቱም የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም÷ ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን በመያዝ ተከሳሹን በሠባት ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ