አዲስ አበባ፣ ግንቦት10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በታንዛንያ ዋና ከተማ ዶዶማ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ አዲስ ሕንፃ ግንባታ መሠረተ-ድንጋይ አስቀመጡ ።
በሌላ በኩል ሚኒስትር ዴኤታዋ ከታንዛንያ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ብርቱካን ከታንዛንያ አቻቸው አምባሳደር ማባሩክ ናሶር ማባሩክ ጋር ባደረጉት ውይይት÷የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሁለቱም ወገን በኩል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ከታንዛንያ የኢሚግሬሽን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አና ማካካላ ጋርም ተወያተዋል፡፡
በዚህ ወቅት አምባሳደሯ ለኢትዮጵያውያን በታንዛንያ የመዳረሻ ቪዛ መፈቀዱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ወደ ተለያዩ መዳረሻ ሀገራት ለሚደረግ ህገወጥ ፍልሰት የታንዛንያን ድንበር አቋርጠው በመግባታቸው ምክንያት በጸጥታ አካላት ተይዘው በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵውያን ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
የታንዛኒያ መንግሥት በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ የኢሚግሬሽን ኮሚሽነሯ አረጋግጠዋል ።