አዲስ አበባ፣ ግንቦት10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሥልጣን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ባለስልጣኑ ባቀረበው በማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሀገራዊ ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ በዶ እንደተናገሩት፤ መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በሁሉም ዘርፍ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለአብነትም የማዲያ፣ የፀረ-ሽብር እና የሲቨክ ማህበራት አዋጆች መውጣታቸውን አንስተዋል።
የሚዲያ ህግ እንደ አዲስ መሻሻሉ በዘርፉ ከዚህ በፊት አሳሪ የነበሩ ህጎችን በመለየት ለዜጎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ብሄርን፣ ቋንቋንና ማህበራዊ እሴቶችን ተገቢ ባልሆነ መልኩ በመጠቀም ለዘመናት አብሮ የኖረ ህዝብን ለማቃቃርና ሀገርን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሰሩ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
ይህንን ለመከላከል ባለስልጣኑ ክትትልና ቁጥጥሩን በማጠናከር ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል።
የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ህግ ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን በማንኛውም የመረጃ ማሠራጫ ጣቢያ ማሠራጨት የሚከለክል እንደሆነ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንና በይዘት እየጨመረ የመጣውን የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ለመከላከል ግንዛቤ የመፈጠር ሥራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንዴሞ የጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የህብረተሰቡን አስተሳሰብ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።