አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁሉም ዘርፍ አቅምን ማሳደግ የፕሮፌሽናል ሠራዊት መገለጫ ባህሪ ነው ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ቢሾፍቱ የሚገኘውን የጦር ሃይሎች ሪፈራል ሆስፒታል በተመረቀበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ መከላከያ ሠራዊት በሪፎርሙ የትግበራ እቅድ መሰረት እያከናዎናቸው ከሚገኙ ስራዎች መካከል አንዱ የጤናው ዘርፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዘርፉ ከተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች አንዱ በቢሸፍቱ የሚገኘው የጦር ሃይሎች ሪፈራል ሆስፒታል መሆኑን ጠቅሰው፤ ሆስፒታሉ የሰራዊቱን የጤና ዝግጁነት አቅም እያሳደገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሆስፒታሉ አሁን ላይ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው የሚታከሙ ታማሚዎች በሀገር ውስጥ እንዲታከሙ የሚያስችል መሆኑን እና ይህም ከሀገር ለመወጣት የሚከፈለውን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያድን አስገንዝበዋል፡፡
በሁሉም ዘርፍ አቅምን ማሳደግ የፕሮፌሽናል ሠራዊት መገለጫ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ መከላከያ በመሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ እየሰራ ያለው ስራ ከተቋሙ ባለፈ ለተሻለ ሀገር ግንባታ ሞዴል የሚሆን ነው ብለዋል።
የሆስፒታሉ ግንባታ ሰራዊቱ በጦር ሜዳ ከማሸነፍ እና የሀገርን ክብር ከማስጠበቅ በተጨማሪ በማንኛውም ስራ ውጤት ማምጣት የሚችል ሰራዊት መሆኑን ማሳያ ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቢሾፍቱ የተገነባው የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ መመረቁ ይታወቃል።