አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖን በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ መርቀው ከፈቱ።
በመርሃ-ግብሩ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎች፣ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥራን ለማሳካት ትብብር ይጠይቃል።
በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ጅምር የፈጠራ ሥራዎችን መመልከታቸውን ገልፀዋል።
የስማርት ከተማ ግንባታን የሚያፋጥኑ፣ የኃይል ሥርጭትን በትክክል ለተጠቃሚ የሚያደርሱና ብክነትን የሚቀንሱ ስታርት አፖች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የዳታ ማዕከላት መኖራቸውም ለሀገር ትልቅ ጥቅም ነው ብለዋል።
ዳታ ማዕከላቱን የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በአግባቡ በመጠቀም መረጃን ማከማቸትና ለሀገር እድገት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዓለም አብዛኛው ሀብቷ ወደ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እየገባ መሆኑን መረዳትና በዚያው ልክ ተጠቃሚ የሚያደርግ የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሒሳብና ሳይንስ ያላቸውን ልዩ ችሎታ ለመጠቀም፣ መንግሥት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂና ኮምፒውተር ፕሮግራም አበልፃጊዎችን (ኮደርስ) ማሰልጠን የሚያስችል ኢንሼቲቭ እንደሚያስጀምር ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂን ለራሱና ለሀገር ጥቅም የሚያውል ትውልድ መፍጠር አለብን ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስትራይድ ኢትዮጵያ ሀገሪቱ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የያዘችውን ግብ ለማሳካት ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ገልፀዋል።
ኤክስፖው ከኢትዮጵያ ወጥቶ ቀጣናዊ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ስለመሆኑም ጠቁመው፤ በዚህ ኤክስፖ የመንግሥትና የግሉ ተቋማት የትምህርት ተቋማት ስታርት አፖች ይመካከራሉ ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ይኸው ኤክስፖ “ሳይንስ በር ይከፍታል፤ ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፤ ፈጠራ ወደፊት ያራምዳል” በሚል መሪ ሃሳብ ከግንቦት 10 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።