የሀገር ውስጥ ዜና

10ኛው ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና ተጀመረ

By Melaku Gedif

May 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰላም ሚኒስቴር የተዘጋጀው 10ኛው ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መሰጠት ጀምሯል።

“በጎነት ለአብሮነት” በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ወር የሚሰጠውን ስልጠና ሚኒስቴሩ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መሆኑ ተመላክቷል።

በስልጠናው ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶቾ እየተሳተፉ መሆኑን የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ጀማል ገልጸዋል።

ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማሕበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ዋና ዓላማ ለወጣቶች የሀገርና የሕዝብ ፍቅርን ከማላበስ ባለፈ ምክንያታዊ እንዲሆኑና የሕይወት ክሕሎታቸውን ማሳዳግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የሥራ ባሕልን፣ ሥነ ምግባር እና የሰላም እሴትን በማጎልበት ሀገራዊ አንድነትን፣ ብሔራዊ መግባባትን እና ጥልቅ ማሕበራዊ ትስስርን የማስፈን ዓላማ እንዳለው አስረድተዋል።