የሀገር ውስጥ ዜና

የአውስትራሊያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ያለመ ምክክር ተደረገ

By Feven Bishaw

May 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውስትራሊያ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ልምድ ያካበቱ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መሰማራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው÷ ባለሀብቶቹ በሪል ስቴት ግንባታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተለያዩ ሀገራት የካበተ ልምድ አላቸው፡፡

በኢትዮጵያም በመኖሪያ ቤት ግንባታ እና በመንገድ ሥራ ለመሠማራት ፍላጎት እንዳላቸው ባለሃብቶቹ ማሳወቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ወ/ሮ ጫልቱ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት በመሠረተ-ልማት በተለይም በኮንስትራክሽ ኢንዱስትሪው ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂና የካበተ ልምድ ይዘው ከሚመጡ ባለሀብቶች ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

በተለይም በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና በመንገድ ዘርፍ ትኩረት ሰጥተው ወደ ስራ ለመግባት ፍላጎት ከሚያሳዩ የግልም ሆነ የመንግስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በትብብር ለመሥራት መንግስት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡