የሀገር ውስጥ ዜና

2ኛው ዓለም አቀፍ የደቡብ ደቡብ ትብብር ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

By Melaku Gedif

May 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የደቡብ ደቡብ ትብብር ጉባዔ “የደቡብ ደቡብ ጉባዔ ዓለም አቀፍ የደቡብ ትብብርን በዘላቂነት ያሳድጋል” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት ጉባዔው÷ ያልተማከለ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም፣ ዘላቂ የልማት ተሞክሮን፣ ፈጠራና እውቀትን በመጋራት ዓለም አቀፍ ደቡብ ደቡብ ትብብር ለማጎልበት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ዓለም አቀፍ አጋሮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የቴክኖሎጂና ስራ ፈጣሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራን ጨምሮ ጉባዔው ከ500 በላይ ተሳታፊዎችን የሚያሰባስብ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከአፍሪካ ሀገራትና ህንድ የመጡ ሙያተኞችም በፀኃይ የኃይል የሚሰሩ የታዳሽ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ግኝቶቻቸውን የሚያሳዩበት ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተዘጋጅቷል።

የተገለሉ ማህበረሰቦችን በዘላቂነት በዕውቀት በቁሳቁስ ማብቃት፣ በታዳሽ የኃይል አማራጭ የተደገፈ ዘላቂ የኢኮኖሚያዊ የመተዳደሪያ ዕድልን መክፈትና የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅም መገንባት የጉባዔው ዋና ዋና ትኩረቶች መሆናቸው ተመላክቷል።