የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በዶሃ የሠራተኛ ዝውውር ዓለም አቀፍ ትስስር መድረክ ላይ እየተሳተፈች ነው

By Melaku Gedif

May 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በኳታር ዶሃ እየተካሄደ በሚገኘው የሠራተኛ ዝውውር ዓለም አቀፍ ትስስር መድረክ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡

መድረኩ በባህረ ሰላጤው ሀገራት እና በአፍሪካ ሠራተኛ ላኪ ሀገራት መካከል ያለውን የሰራተኛ ዝውውር ትስስር ለማሳደግ እና በትብብር ለመስራት ያለመ ነው መባሉን በዶሃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።

በመድረኩ የ33 ሀገራት የሰራተኛ ሚኒስትሮች፣ የዓለም የስራ ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ የባህረ ሰላጤው የትብብር ም/ቤት አባል እና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል፡፡

መድረኩ በተሳታፊ ሀገራት መካከል አጠቃላይ የውይይት መድረክ ለመፍጠር ያለመ ሲሆን÷ በዚህም ቀጣናዊ የትብብር ጥረቶችን እና አጋርነትን ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማሳካት ሀሳቦችና ልምዶችን የሚለዋወጡበት መሆኑን ተገልጿል።

ኢትዮጵያን በመወከል በሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ዳንኤል ተሬሳ የተመራ ልዑክ እና በኳታር፣ በየመን እና በኢራን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አምባሳደር ፈይሰል አልይ አብራሂም ተሳትፈዋል፡፡