አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ለተደረገው የ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለፀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫ፥ ሚኒስቴሩ ለ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ 20 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እስካሁን 14 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማሰባሰቡን ገልጸዋል፡፡
ለንቅናቄው መሳካት ግምታቸው 22 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የሚሆኑ 15 ሞዴል መጸዳጃ ቤቶችን በራሳቸው ለመገንባት ቃል የገቡ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላትም እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡
በአዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ንቅናቄውን ማገዝ የሚፈልጉ ከሆነ እንደሚበረታቱ ገልጸው፥ ለንቅናቄው ድጋፍ የማሰባሰብ ጥረት እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ከሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ የሚደረገውን እንቅስቃሴም በሚመለከት እስካሁን ከ27 ሺህ በላይ ፍልሰተኞችን መመለስ ተችሏል ተብሏል፡፡
በአራት ወራት ውስጥም 70 ሺህ ፍልሰተኞችን ለመመለስ ከተያዘው እቅድ አንጻር 35 በመቶ ያህሉ እንደሆነና እቅዱን በሙሉ ለማሳካትም ርብርቡ ተጠናክሮ እንደቀጠለም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
#ጽዱኢትዮጵያ