የሀገር ውስጥ ዜና

ም/ጠ/ሚ ተመስገን የምግብና ስርዓተ ምግብ ዕቅዶች አፈጻጸምን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያዩ

By Feven Bishaw

May 23, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በምግብ እና ስርዓተ ምግብ፣ በሰቆጣ ቃልኪዳን እና በጤና መድህን ላይ የተያዙ ዕቅዶች እና አፈፃፀማቸውን በተመለከተ ዛሬ ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች የማህበረሰቡን ጠቀሜታ ከፍ ያደረጉ እና ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተሞክሮዋን ማጋራት የጀመረችባቸው መሆናቸውን አይተናል ብለዋል።

ተግባራቱ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፣ የአጋዥ አካላት እንዲሁም የህዝቡን ትብብር፣ ድጋፍ፣ ትጋት እና ቁርጠኛ ተሳትፎን የሚጠይቁ በመሆናቸው ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ በውይይታችን ተግባብተናል ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት እና ፅዱ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ሀገራዊ ፕሮግራሞች ከተግባራቱ ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳላቸው በመጠቆም፤ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅም በውይይቱ መታየቱን ገልጸዋል፡፡