አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የብሪክስ ብሔራዊ የሚኒስትሮች አስተባባሪ ኮሚቴ ሁለተኛውን ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።
የስብሰባው ዓላማ ኢትዮጵያ በብሪክስ ስብስብ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ መገምገም እና ቀጣይ ስራዎች ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነዉ ተብሏል።
የኮሚቴው ሰብሳቢና የኢትዮጵያ የብሪክስ ብሔራዊ ተወካይ አቶ ማሞ ምህረቱ÷ ኢትዮጵያ በብሪክስ እንቅስቃሴዎች ላይ የምታደርገው ንቁ እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች፣ ለሀገራዊ ልማት ግቦች መሳካት እና ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መጠናከር ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል።
ኮሚቴው ኢትዮጵያ በተሳለጠ ሁኔታ ወደ ብሪክስ እንድትቀላቀል የሚያስችለው የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ ስትራቴጂ ላይም ተወያይቷል።
በብሪክስ ስብስብ የመግባቢያ ስምምነት እና የኢትዮጵያ ድጋፍ መግለጫ ላይም መምከሩን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ የብሪክስ ስብስብ አባልነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትብብር፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ያጠናክራልም ተብሏል።