የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ 171 ህገ-ወጥ ሉኳንዳ ቤቶች ላይ ዕርምጃ ተወሰደ

By Meseret Demissu

June 14, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ 171 ህገ-ወጥ ሉኳንዳ ቤቶች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

እርምጃ የተወሰደባቸው ሉካንዳ ቤቶች ከቄራ ድርጅት ውጪ እርድ እየፈጸሙ ለህብረተሰቡ ሲሸጡ የነበሩ እንደሆኑ ተገልጿል።

በከተማ አስተዳደሩ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ ÷ ከተማ አስተዳደሩ ከኮቪድ-19 ስርጭት ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ባደረገው አሰሳ  በምግብ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ንክኪዎችና የጽዳት ችግሮች እንዳሉ ተመልክቷል።

በከተማዋ ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ ሉኳንዳ ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከነዚህም በህጋዊና በትክክለኛ መንገድ አገልግሎት የሚሰጡ እንዳሉ ሁሉ በአንጻሩ ለኮቪድ-19 ስርጭትና ለሌሎችን በሽታዎች አጋላጭ የሆኑ እንዳሉም ተደርሶባቸዋል።

እነዚህ ህገ ወጥ ሉኳንዳዎች በበግና በፍየል የእርድ አገልግሎት ዙሪያ 90 በመቶ የሚሆነው አስፈላጊው ምርመራ ሳይደረግለትና ወደ ቄራ ሳይገባ የእርድ አገልግሎት ሲሰጡ ነበር።

በቀንድ ከብት እርድም 30 በመቶ የሚሆነው አገልግሎት ከቄራ አገልግሎት ውጪ በህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ንጽህናው ባልተጠበቀ እርድ ተፈጽሞ ለህዝቡ እየቀረበ መሆኑ ታውቋል።

በዚህም ሳቢያ ከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ከግብር  ገቢ እና ከቄራ አገልግሎት በአማካይ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱ ተገልጿል።

በመሆኑም ጤንነቱ ያልተረጋገጠ ስጋ ሽያጭ የሚያከናውኑ 132 ሉኳንዳ ቤቶች ላይ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

በ360 የሚሆኑ ህግ-ወጥነታቸው የተረጋገጡ ታርደው ለአገልግሎት የቀረቡና በመታረድ ላይ ያሉ እንዲሁም ለመታረድ ዝግጁ የነበሩ በግና ፍየሎችን እንዲሁም 50 የቀንድ ከብት ተይዟል።

ይህንንም ሲፈጽሙ የነበሩ የ132 ሉኳንዳ ቤቶች ላይ ስጋውን የመውረስ ነጋዴዎቹ ላይም የእስር እርምጃ የተወሰደ ሲሆን 39 ሉኳንዳ ቤቶች ደግሞ እንዲታሸጉ ተደርጓል።

በመሆኑም እንደነዚህ ያሉ ተግባራት ከህገ-ወጥነታቸው ባሻገር ለጤና ችግር የሚያጋልጡ ከመሆናቸው አንጻር ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ህገ-ወጦችንም በማጋለጥ እንዲተባበር ጥሪ መቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።