የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ጥላሁን ከበደ ባለሀብቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ

By ዮሐንስ ደርበው

May 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ባለሀብቶች፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና የመንግሥት አካላት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ የ2016/17 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ክልላዊ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ ‘መርካቶ ዩሾ’ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡

አቶ ጥላሁን በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ፍቅር፣ ሰላምና ይቅርታን መሰረት አድርገን በመተጋገዝ ሰርተን ብልፅግናችንን ማረጋገጥ እንችላለን ብለዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ከያዛቸው አራት መሠረታዊ መርሐ-ግብሮች አንዱ በማኅበራዊ ዘርፍ ሰው ተኮር ተግባራትን ማከናወን መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የበጎነት ተግባር ሥር ሰዶ እና ባህል ሆኖ ዜጎችን እንዲጠቅም ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማሳሰባቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

በበጎ ፈቃድ ዘርፍ የጀመርናቸው ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው ያሉት አቶ ጥላሁን÷ አሮጌውን ዓመት ስናጠቃልል እና አዲሱን ዓመት ስንጀምር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብሩ በክልል ደረጃ መጀመሩን አስታውቀው÷ ባለሀብቶች፣ በየደረጃው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና የመንግሥት አካላትም ይህን ተግባር እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡