የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት በሚሠራቸው ተግባራት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

May 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል የልማት ሥራዎችን ለማጎልበትና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚያከናቸው ተግባራት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

በሐረሪ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምክክር መድረክ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

አቶ ኦርዲን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ውይይቱ በክልሉ በሚከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ በሕዝቦች አብሮነትና ሌሎች በክልሉ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም አስረድተወል፡፡

የተጀመሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራዎችን ለማጎልበት፣ በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ ያሉ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ውስንነቶችን ለመፍታትም መድረኩ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።