የሀገር ውስጥ ዜና

በጅግጅጋ ሲካሄድ የነበረውን የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ

By Feven Bishaw

May 29, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቀቀ።

በመድረኩ ላይ የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን፣ በብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ መሀመድ ሻሌ (ኢ/ር) እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በምክክሩ ላይ ዘመናዊ ገበያ በመፍጠርና የእንስሳት ንግድና ገበያን በማሳለጥ እንዲሁም በክልሉ ያለውን እምቅ የግብርና ልማትን በማጠናከር ህዝቡ ከተረጂነት እንዲላቀቅ አመራሩ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት የእርዳታ ጥገኝነት ጉዳትን ከሀገር ሉአላዊነትና ሁለንተናዊ ብልፅግና አንጻር በጥልቀት በመረዳት ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት መስራት እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ መሀመድ ሻሌ (ኢ/ር)÷ በወንዞችና ተፋሰስ አካባቢዎች ያልታረሱ ለም መሬቶችን በመጠቀም እንዲሁም በመስኖና በዝናብ በማልማት የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ መሠራት እንዳለበት ገልፀዋል።

መድረኩ ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን አመራሩ እንዲተገብር መመሪያና አቅጣጫ በመስጠት ተጠናቋል።