አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ አካላት ከጣልቃ ገብነት ነፃና ገለልተኛ ሆነው በመስራት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ አስገነዘቡ፡፡
ሀገራዊ የፍርድ ቤቶችና የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
አፈ-ጉባዔው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን በማድረግ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ፍትሕ መስፈን፣ ለሠላም እና ማኅበራዊ ኢኮኖሚ ልማት ዋስትና መሆን እንዲችል ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩም የፍርድ ቤቶች፣ የፍትሕ ዘርፍ ተቋማት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቴክኒክ ኮሚቴና የሀገራዊ የፍርድ ቤቶችና የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሚሽን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የመስክ ምልከታ ሪፖርት ቀርቧል።
በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ መገለጹንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡