የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሌጁ የተገነባ ሠራዊት ለመፍጠር የሚያከናውነው ተግባር የሚደነቅ ነው-ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

By Mikias Ayele

May 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሜጀር ጄኔራል ሙልጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባለው ውስን አቅም ችሎታውና እውቀቱ የተገነባ ሠራዊት ለመፍጠር የሚያከናውነው ተግባር የሚደነቅ ነው ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን በዛሬው ዕለት የጎበኙ ሲሆን ኮሌጁ የተሻለና ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ የሚያስችል ምክክርም አካሂደዋል።

በዚህ ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ÷ ሠራዊቱ በታጠቀው መሳሪያ ላይ የተሻለ አቅምና እውቀት እንዲኖረው ከሚያስችሉ ኮሌጆች መካከል ብቸኛው ኮሌጅ የሜጄር ጀኔራል ሙልጌታ ቡሊ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁን መደገፍና ያሉበትን ችግሮች መቅረፍ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት ኤታማዦር ሹሙ÷ኮሌጁ የማሰልጠን አቅሙን ወደ ዲጂታል መቀየር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል አበበ ዋቅሹማ በበኩላቸው÷ኮሌጁ ከተመሠረተ ጀምሮ በርካታ ወታደር ሙያተኞችን ከሀገር ውስጥ እስከ ጎረቤት ሀገር ድረስ ማሰልጠኑን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ያለበትን የመማር ማስተማር ችግር መቅረፍ ከተቻለ በሙሉ አቅሙ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን ይችላል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡