የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል በመስኖ ሊለማ ከሚችለው ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ 9 በመቶ ያህሉ ብቻ ለምቷል

By Tibebu Kebede

June 15, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል በመስኖ ሊለማ ከሚችለው 1 ሚሊየን 75 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 9 በመቶ ያህሉ ብቻ መልማቱን አንድ ጥናት አመላከተ።

መሬቱ በሚፈሱ ወንዞች የሚለማ ሲሆን ውሃ ካገኘ ሊለማ የሚችል 8 ሚሊየን ተጨማሪ ሔክታር መሬትም በክልሉ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና በክልሉ ውሀ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ቅንጅት የተካሔደው ጥናት ከ32 በላይ ባለሙያዎችንና ምሁራንን ያሳተፈ ነበር ተብሏል።

ለሁለት አመታት ቆይታ ያደረገው ጥናት በክልሉ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል መሬትና የውሃ መጠንን በሚገባ ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን፥ ያለውን የውሀ ሀብትም በሚገባ መጠቀም እንዳልተቻለም ጥናቱ አሳይቷል።

በተጨማሪም በክልሉ ያለን ሀብት በሚገባ አውቆ መጠቀም ላይ ክፍተት መኖሩንም ጥናቱን ያቀረቡት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ምህረት ዳናንቶ ተናግረዋል።

47 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል የከርሰና የገፀ ምድር ውሃ በክልሉ እንደሚገኝና ይህን በአግባቡ መጠቀም ቢቻል ከክልሉ አልፎ ለሀገሪቱም ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የደቡብ ከልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው፥ በክልሉ ያለን የውሃ ሀብት በመጠቀም ከፍተኛ እርሻዎችን ወደ መስኖ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ጥናቱ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

በሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ቢደረግም በምግብ ራስን ለመቻል አዳጋች ከማድረጉም በላይ ስንዴ ከውጭ ከማስመጣት ጀምሮ በክልሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጋ እርዳታ ፈላጊ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ክልሉ ይሄን ያህል ሀብት እያለው ለችግር መጋለጡ ተገቢ አይደለም ያሉት ሃላፊው፥ ግብርና ማቀነባበሪያዎችን ማጠናከር እና ምርት ወደ ውጭ ለመላክ መስኖ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በጥናቱ የተገኙ ውጤቶች ተግባራዊ እንዲሆኑም በቀጣይ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ሃላፊው።

ጥናቱ በዋናነት የባሮ – አኮቦ፣ የገናሌ – ዳዋ፣ የኦሞ – ጊቤ እና የሪፍት ቫሊ አራት ታላላቅ ተፋሰሶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በብርሃኑ በጋሻው