የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ከ8 ሚሊየን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሳተፉ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

June 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮ የክረምት ወቅት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ8 ሚሊየን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ተሾመ ፈንታው ተናግረዋል፡፡

በመጪው የክረምት ወቅት ከ8 ሚሊየን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ ግብ መያዙን ገልጸው÷ ከነዚህ መካከል ከ 5 ሚሊየን የሚልቁት ወጣቶች እንደሚሆኑ አመላክተዋል፡፡

በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ተሳታፊ ወጣቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችም በገንዘብ፣ በቁሳቁስ አቅርቦት፣ በጉልበትና በዕውቀት ከ6 ቢሊየን ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና እድሳት፣ ማዕድ ማጋራት፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ የጤና አጠባበቅ፣ የማጠናከሪያ ትምህርትና ሰላምን ማስጠበቅ ጨምሮ በሌሎችም 14 የሥራ ዘርፎች እንደሚካሄድ አብራርተዋል።

በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወራት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውንም አስታውሰዋል፡፡