የሀገር ውስጥ ዜና

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን አብዮት ጀምረናል- ም/ጠ/ ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By Shambel Mihret

June 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ከተረጂነት የማላቀቅና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን አብዮት ጀምረናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች እና የተቋማት ኃላፊዎች በመድረኩ ተገኝተዋል።

አቶ ተመስገን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አስተዳደርን እና ሀገራዊ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን አዲስ ፖሊሲ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

ከተረጂነት እንውጣ የሚል አብዮት መቀስቀስ የፖሊሲው ዋና ግብ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አደጋን በራስ የመሸከም አቅም ማዳበር እንደሚያስፈልግ አስረድተው÷ በቅድመ አደጋ፣ በአደጋ እና በድህረ አደጋ የሚሰሩ ስራዎች በታቀደው መሰረት በተናበበ መልኩ መከናወን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

እንደሀገር አደጋን በራስ አቅም መቋቋም እንችላለን የሚለውን ትልቅ አብዮት ለማሳካት አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።

ከተረጅነት ለመላቀቅና እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን የባህል ለውጥ እንደሚያስፈልግና ልመናን መፀየፍ እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በፍረህይወት ሰፊው