የሀገር ውስጥ ዜና

260 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ የሳዑዲ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተዋል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By ዮሐንስ ደርበው

June 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሃብቶች 260 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ 233 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ማዋላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በዚህም ለ75 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሰጡት መግለጫ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያን ለኢንቨስት የሚመርጡ ሀገራትና ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱንም አመላክተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ 79 አባላት ያሉት የሳዑዲ ዓረቢያ ከፍተኛ የቢዝነስ ልዑክ በኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝት ለሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት መጎልበት አስተዋፅኦ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በግብርና፣ በማዕድን ዘርፍ፣ በቱሪዝም፣ በኢነርጅ፣ በትራንስፖርት፣ ሎጂስቲክስ እንዲሁም በሌሎች ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያሉትን ዕድሎች ለመገንዘብ የሚያስችል ውይይት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በሳዑዲ ዓረቢያ አቻው መካከል የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙም የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ለማስፋት ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የሀገራቱ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው÷ ለአብነትም በፈረንጆቹ 2022/2023 ኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የላከቻቸው የወጪ ምርቶች 325 ሚሊየን ዶላር ማስገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ80 በላይ አባላት ያሉት የፓኪስታን ኩባንያዎች ልዑክ ለስድስት ቀናት በኢትዮጵያ ያደረገው የቢዝነስ ጉብኝት÷ ለኢትዮጵያና ፓኪስታን ግንኙነት መዳበር አስተዋፅኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

የተወሰኑ ኩባንያዎችም ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የተፈራረሟቸው የመግባቢያ ስምምነቶች ተጨባጭ ውጤት መመዝገብ መጀመሩን አመላካች ነው ብለዋል።

ከሁለቱ ሀገራት የተውጣጡ ከ150 በላይ ባለሀብቶች በሀገራችን ያደረጉት የኢንቨስትመንት ጉብኝት ሚኒስቴሩ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሰጠውን ትኩረት እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ሀገራትና ባለሀብቶች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ያመላክታል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

እንዲሁም ሚኒስቴሩ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ብቻ ለ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማሰባሰቡንና በአጠቃላይ እስካሁን ለንቅናቄው ሞዴል መጸዳጃ ቤቶችን ለመገንባት ቃል የተገባውን ጨምሮ 44 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር እንደተሰበሰበ ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡