የሀገር ውስጥ ዜና

የ”ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” ሩጫ ውድድር የፊታችን ሰኔ 23 ይካሄዳል

By Melaku Gedif

June 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ”ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የሩጫ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ውድድሩን የሰላም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነው በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚያካሂዱት፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)÷ ከስፖርት የበለጠ የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የአንድነት እና የወንድማማችነት ማሳያ የለም ብለዋል።

ሩጫ የኢትዮጵያ የአሸናፊነት መንፈስ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህን የአሸናፊነት መንፈስ ለሰላም ማዋል እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሩጫ ውድድሩ ከስፖርታዊ ውድድር ባሻገር ዜጎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ፣ የአንድነት መንፈስ እንዲያጎለብቱ እና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ማስቻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡

የሩጫ ውድድሩ በኢትዮጵያ እየተገኘ ያለውን አንጻራዊ ሠላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር ዜጎች በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም በህዝቦች መካከል አንድነትን፣ አብሮነትን መቀራረብን እንዲሁም መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት እንደሚያስችል ነው የተገለጸው፡፡

ሩጫው የፊታችን ሰኔ 23 ቀን ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ባሉ ዋና ዋና ከተሞች እንደሚካሄድ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሩጫው የሚሸፍነው ርዝመት በአዲስ አበባ 6 ኪሎ ሜትር ሲሆን ÷ መነሻና መድረሻ መስቀል አደባባይ ሆኖ በሌሎች ከተሞች እንደአካባቢው ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል ተብሏል።