አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ አዲስ ልምምድ እንደመሆኑ መጠን ፅንሰ ሀሳቡ ከሌሎች የሰላም ግንባታ ወይም ከግጭት አፈታት ዘዴዎች ጋር እየተቀላቀለ ብዥታን ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡
የሚከተሉት ነጥቦች ስለ ምክክር ፅንሰ ሀሳብ መሰረታዊ ባህሪያት በአጭሩ ያስረዳሉ፡፡
1. ምክክር እንደ ድርድር ዜጎች ሊያሳኩ በሚያስቧቸው ውስን የሆኑ ፍላጎቶች ላይ ስምምነቶች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ይልቅ ዜጎች ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የሚፈቱበትን መደላድል ይፈጥራል፤
2. ድርድር የሚታዩ ወይም የማይታዩ ይዞታዎችን በማከፋፈል ወይም ለአንደኛው ወገን በመስጠት ግጭትን ለማብረድ የሚያገለግል ሲሆን÷ ምክክር ደግሞ በሰዎች መካከል አዲስ የመከባበር፣ የመተማመን እና የመተባበርን ባህል በማዳበር የዜጎችን ግንኙነት ከፍ ያደርጋል፤
3. በክርክር ውስጥ የሚዘወተረው አንዱ የሌላውን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ የበላይነትን ለማሳየት ሲሆን÷ በምክክር ሂደት ውስጥ ግን ይህ ሁኔታ ፈጽሞ አይኖረም፡፡
በምክክር ሂደት የሚሳተፉ ተሳታፊዎቸ አንዳቸው የሌላኛውን ሀሳብ በአግባቡ በማድመጥ የዚያን ሰው ሀሳብና ፍላጎት ለመረዳት ጥረት ያደርጋሉ፤ በሂደቱም የጋራ የሚሉትን እና የሚያግቧቧቸውን መፍትሔዎች ያመነጫሉ፡፡