አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ከተረጂነትና ተመጽዋችነት በማውጣት ወደ ምርታማነትና የተሟላ ሀገራዊ ክብር ለማሻገር መንግስት በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ በብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ፣ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃብታሙ ካፍት እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ከሚዛን አማን ከተማ እና አካባቢው የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ሃብት ያላት ሀገር ናት፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ሲል እጃችንን ወደ ሌሎች ከመዘርጋት ይልቅ በራሳችን ሰርተንና አምርተን ሉዓላዊነታችንና ክብራችንን ለመመለስ ነው ብለዋል።
ጊዜው ተረባርበንና ተቀናጅተን የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማረጋገጥ ከተመጽዋችነት ወደ መጽዋችነትና ብልፅግና ማማ ለመውጣት ፓርቲያችን በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍት በበኩላቸው÷ የልመናን አስከፊነት ህብረተሰቡ በመገንዘብ ድህነት ላይ ለመዝመት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
የልማት መስተጋብሮችን በተግባራዊ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገርን እንጂ ልመናና ድህነትን ልናወርስ አይገባም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡