የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አህመድ ሽዴ ከኳታር የገንዘብ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

By Melaku Gedif

June 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከኳታር አቻቸው አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና በኳታር በፋይናንስ፣ በልማት ትብብር እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ መክረዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት አቶ አህመድ ሽዴ፤ የኳታር ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ሊሳተፉ የሚችሉባቸው የኢንቨስትመንት ዕድሎች በስፋት መኖራቸውን ገልጸዋል።

በተቋም ለተቋም ግንኙነት በትብብር ለመስራት ከስምምነት የደረሱ ሲሆን በቀጠናዊ እንዲሁም በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ በትብብር ለመስራት ከሥምምነት መድረሳቸውን በዶሃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።

የኳታር የልማት ፈንድ በኢትዮጵያ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች እንዲጠናከሩና ተጨማሪ ትብብሮችን መፍጠር እንዲቻል የቴክኒካል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክና አጠቃላይ ያሉትን ፍላጎቶች በመለየት ወደስራ ለመግባትም ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።