አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰኔ 4 እና 5 ቀን 2016 ዓ.ም ሲሰጥ የነበረው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)÷ፈተናው እንዲጠናቀቅ አስተዋጽአ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የፈተናውን ወረቀት ከማጓጓዝ ጀምሮ ተማሪዎች ተፈትነው እስከሚያጠናቅቁ ድረስ የተሳተፉ የፀጥታ አካላት፣ የትምህርት አመራሮች፣ ወላጆች፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላትና ተማሪዎችን አመስግነዋል፡፡
በቀጣይ ሰኔ 13 እና 14 ቀን 2016 የሚሰጠው የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውንም የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአማራ ክልል184 ሺህ 393 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተናውን እንደወሰዱ ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበበ ከተማ አሥተዳደር ለሁለት ቀናት የተሰጠው ከተማ አቀፍ የ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መጠናቀቁን የአሥተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ጋምቤላ ክልሎች ከትናንት ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና መጠናቀቁን የየክልሎቹ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡