አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዕቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ፡፡
ከ2013 እስከ 2015 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትና የ2016 በጀት ዓመት የአስፈጻሚ ተቋማት የተጠቃለለ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተጠናቅቋል፡፡
አቶ ኡሞድ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷የሚታቀዱ ዕቅዶችን አፈፃፀም መከታተል እና መቆጣጠር እንደሚገባ በመግለጽ ውጤት ተኮር ሥራ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የታቀዱ ዕቅዶችን ተግባራዊ በማድረግም የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ተቋማት በይበልጥ በማጠናከር፤ ክፍተት ያለባቸውም በቀጣይ በማረም ውጤት ተኮር ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል፡፡