አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “የአባቶች ሚና በልዩነት ለተዋበ ጠንካራ የህዝቦች አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተወያዩ ነው፡፡
በውይይቱ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ በክልሉ ከሚገኙ ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የክልሉን ህዝብ በማስተባበርና በክልሉ የሰላም እና የልማት ጉዳዮች በንቃት በማሳተፍ ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በመስራት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
በተለይ ለሰላም ልዩ ትኩረት በመስጠት ከክልሉ ምስረታ ማግስት ጀምሮ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድርግ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ በመሰራቱ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉ ተገልጿል፡፡
ይህ ውይይትም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑ የተገለፀ ሲሆን÷ በክልሉ ሰላምና ልማት ዙሪያ በመነጋገር የክልሉን ሰላም ለማጽናት እና ሁሉን አቀፍ ልማት ለማረጋገጥ ተቀራርቦ በዘላቂነት አብሮ ለመስራት የሚያስችል የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያግዛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡