አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንድ ከቻይና ጋር በድንበር አካባቢ በተፈጠረ ግጭት 20 ወታደሮቿ ተገድለውብኛል አለች።
የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በምዕራባዊ ሂማሊያ አካባቢ ከቤጂንግ ጋር በተፈጠረው ግጭት ወታደሮቹ እንደተገደሉበት አስታውቋል።
ወታደሮቹ በሂማሊያ ተራሮች ከፍተኛ ቦታ ላይ ግዳጅ ላይ በነበሩበት ወቅት መገደላቸውንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
በወቅቱ በሃገራቱ ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ አለመደረጉ የተነገረ ሲሆን፥ በተፈጠረ አለመግባባት የጨበጣ ውጊያ ማድረጋቸው ተገልጿል።
በዚህ ሂደትም የተወሰኑ ወታደሮች ከተራራው ተገፍተው አልያም በአጋጣሚ ወድቀው ህይወታቸው አልፏልም ነው የተባለው።
ሚኒስቴሩም ቻይና ሁለቱ ሃገራት በስፍራው የገቡትን ስምምነት በመጣስ የህንድን ሉዓላዊነት ተዳፍራለች ሲል ኮንኗል።
ቻይና በበኩሏ ለተፈጠረው ግጭት ህንድን ወቅሳለች፤ በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት ደርሶብኛል ያለችው ቻይና ዝርዝሩን ከመግለጽ ግን ተቆጥባለች።
ሃገራቱ አሁን የገቡበት ፍጥጫ ከረጅም አመታት በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዘራ