የሀገር ውስጥ ዜና

የፖሊስ ጀልባዎችን ለማሰራት የውል ስምምነት ተፈረመ

By Feven Bishaw

June 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ፈጣን የፖሊስ ጀልባዎችን ለማሰራት ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚህ ጊዜ ÷ፈጣን የፖሊስ ጀልባዎችን ማሰራት ያስፈለገው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆኑ የተጠናከረ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም በውሃ አካላት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል የፖሊስ ኃይል (የኮስታል ጋርድ) ማደራጀቱንም ገልፀዋል።

የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ኃ/ማርያም በበኩላቸው÷በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሚኖረው ፖሊሳዊ ተልዕኮ ተጨማሪ ትጥቅ የሚሆን ፈጣን የፓትሮል ጀልባ ለመስራት ከፍተኛ ጥናት በማድረግና በተደጋጋሚ ለውይይት በማቅረብ በባለሙያዎች መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በውል ስምምነቱ በተቀመጠው ጊዜና ዲዛይን መሠረት ጀልባዎቹን ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተው በቀጣይም ለሌሎች ከተሞች እና ሎጆች እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ፈጣን የፖሊስ ጀልባዎቹን በሚፈለገው ደረጃ እና ጥራት ለመስራት የጣሊያን ባለሙያዎችን በአማካሪነት እንደሚሳተፉ በውል ስምምነቱ ፊርማ ወቅት ተገልጿል፡፡