አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዘመናት ዓለምን ያስደነቀው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሲሸልስ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር እና የአፍረካ ህብረት ቋሚ ተወካይ ካንግ ጁንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ፤ ታሪካዊ ግንኙነት የነበራቸው ሁለት ሀገራት የቀደመውን ግንኙነት በማደስ በወታደራዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የበለጠ በትብብር እና በጥምረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)÷ ከወዳጆቻችን ጋር በጋራ ለመስራት በእቅድ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደር ካንግ ጁንግ በበኩላቸው÷ የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ታሪክ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር የተቆራኘ መሆኑን በመግለጽ ሀገራቸው አሁን ለደረሰችበት ቁመና የኢትዮጵያ ወታደሮች የከፈሉት ዋጋ ሁልጊዜም ሲዘክረው የሚኖር ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በጋራ መስራት፣ ተሞክሮ መለዋወጥ እና ወታደራዊ ትብብር ማድረግ የሚበረታታ ተግባር ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡