አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖችን አስመረቀ።
በምረቃ መርሐ-ግብሩ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፣ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ያስመረቃቸው የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ መኮንኖች በአራት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ÷በስነ ወንጀልና በወንጀል ፍትህ፣ በሰላምና የህዝብ ደህንነት ጥናት፣ በአስተዳደር እና የለውጥ አመራር እንዲሁም በደህንነት ዘርፍ አስተዳደር የሰለጠኑ መሆናቸውም ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው በደህንነት ዘርፍ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ አስተምሮ ማስመረቁም በዚሁ ወቅት መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ፖሊሳዊ ሳይንስ፣ በስነ-ወንጀልና ወንጀል ፍትሕ እንዲሁም በፖሊስ መኮንንነት ዘርፍ አስፈላጊውን ሙያና እውቀት የጨበጡ መሆናቸውም ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ሰልጣኞች መካከል ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 12 የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን የፖሊስ ሰልጣኞች ይገኙበታል።