የሀገር ውስጥ ዜና

ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጎበኙ

By Melaku Gedif

July 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም እና የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየሰጡ ያለውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

የዘንድሮው ክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ መጀመሩ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም በጎ ፈቃደኞቹ እያከናወኑ ያሉትን የአረጋውያን ቤት እድሳት፣ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅትና የችግኝ ተከላ ሥራዎች መመልከታቸውን አዜአ ዘግቧል፡፡

አቶ ብናልፍ አንዱአለም በወቅቱ እንዳሉት÷ በመርሐ ግብሩ 20 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

መርሐ ግብሩ ተማሪዎቹ አብሮነታቸውንና ሀገራዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑንም ጠቁመዋል።