አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ እያካሄዱት ያለው ድርድር ትናንትናም ቀጥሎ ውሏል።
የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በቪዲዮ በቀጠለው ውይይት ሀገራቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት እና ዓመታዊ ስራ ላይ በማተኮር ተደራድረዋል።
ከሚኒስትሮቹ ውይይት ቀደም ብለው የሀገራቱ የቴክኒክና የህግ ቡድኖች በተናጥል በመነጋገር የደረሱበትን ሪፖርት አድርገዋል።
ከቴክኒክ አንፃር መሰረታዊ የተባሉ ጉዳዮች በድርድር መፈታታቸውን ያመለከተው መግለጫው ሆኖም ሙሉ ስምምነት ሆኖ ለመውጣት ግን ከህግ አንፃር ያሉት ጉዳዮች መፈታት አለባቸው ነው ያለው።
የሱዳን ተደራዳሪዎች እስካሁን የተገኘውን ለውጥ ለጠቅላይ ሚኒስትራቸው ማሳወቅ እና መመካከር እንደሚፈልጉ በማሳወቃቸው ድርድሩ ሱዳናውያኑ ተመካክረው ከተመለሱ በኋላ ለመቀጠል ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ብድርድሩ የህዳሴ ግድብ ስራውን ፍፁም በሆነ መልኩ እንዲያከናውን ከሚያስችል ስምምነት ከመድረስ ባለፈ ኢትያጵያ በአባይ ውሃ ላይ ቋሚ የሆን የመጠቀም መብቷን እንዲያረጋግጥ ብልሃት እንደሚፍልግ ጠቁሟል።
በተመሳሳይም የሱዳን እና ግብፅ መንግስታት የሁሉንም ሀገር ሉዓላዊነት እና የጋራ ተጠቃነትን የሚያረጋግጥ ዘላቂ ትብብር የሚፈጥርን መንገድ ሊይዙ እንደሚገባ አመልክቷ።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተደረሰው የመርህዎች ስምምነት መሰረት አሁንም ግድቡን ውሃ የመሙላት መብት እንዳላት አስታውቋል።