አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድ ሥርዓትን ተላልፈው የተገኙ 21 ሺህ የንግድ ተቋማት እንደታሸጉ፣ ምርታቸው ከገበያ እንዲሰበሰብና ሌሎች እርምጃዎች እንደተወሰደባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ እንዳሉት÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመዲናዋ በሚገኙ ከ400 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል።
በዚህም ልዩ ልዩ የንግድ ሥርዓቶችን ተላልፈው በተገኙ ከ50 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
ከዚህ ውስጥ 21 ሺህ የንግድ ተቋማት እንዲታሸጉ፣ ምርታቸው ከገበያ እንዲሰበሰብና ሌሎች ተመሳሳይ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው መደረጉን አስረድተዋል።
ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድና ፈቃድ እድሳት አለማድረግ፣ ለንግድ የሚቀርቡ ምርቶች ተገቢውን ጥራት አለመጠበቅ እንዲሁም ለምርቶች ተገቢውን የዋጋ ዝርዝር በግልጽ አለማስቀመጥ ተቋማቱ ከተላለፏቸው የንግድ ሥርዓቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ጎን ለጎንም በከተማዋ ጤናማ የሆነ የንግድ ሥርዓትን ለማጎልበትና የንግድ ሕጉን በአግባቡ የሚተገብር ነጋዴ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መከናወኑን ለኢዜአ ተናግረዋል