የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ ጫና ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት እየተሰራ ነው

By Feven Bishaw

July 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ ጫና ያለባቸው አካባቢዎች ተለይተው የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት÷ በክልሉ ሁሉም ዞኖች የወባ ስርጭት እንዳለ ጠቅሰው፤ 34 ወረዳዎች ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸው መለየቱን ጠቁመዋል።

በክልል ደረጃ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ለ186 ሺህ 133 ሰዎች የወባ በሽታ ምርመራ ተደርጎ 55 ሺህ 562 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡን ገልፀዋል።

ለታማሚዎችም ተገቢው ህክምና እየተሰጠ እንደሆነ ተናግረው፤ ህክምና ከመስጠት ጎን ለጎን የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

በዚህም በ50 ወረዳ ለ1 ሚሊየን 236 ሺህ 286 ሰዎች አጎበር መሰራጨቱን እና በስምንት ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት መከናኑን ገልጸዋል።

በአንድ ወር ውስጥ በ81 ሺህ 370 ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት መካሄዱን ገልጸው፤ አሁንም የኬሚካል ርጭቱን ለማዳረስ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም 840 ሺህ 239 ካሬ ሜትር ቋሚ እና 843 ሺህ 751 ካሬ ሜትር ጊዜያዊ የወባ መራቢያ አካባቢዎች ተለይተው የማዳፈን ስራ እንዲሁም የበሽታው ማስተላለፊያ ዕጭ መግደያ ኬሚካል ርጭት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩልም በክልሉ ባሉ 13 ሆስፒታሎች፣ 125 ጤና ጣቢያዎች፣ 744 የጤና ኬላዎች ግብአቶች በማሟላት የወባ በሽታ ህክምና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ 301 ሺህ 360 ታማሚዎችን የሚያክም የወባ መድሃኒት በስድስቱም ዞኖች ለሚገኙ ጤና ተቋማት ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

በክልሉ የመድሃኒት እጥረት ባይኖርም በተወሰነ መልኩ የኬሚካል እና የአጎበር እጥረት መኖሩን አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ በሽታውን ለመካለከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ በመሰራቱ ስርጭቱ በተወሰነ መልኩ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

ስለ በሽታው መንስዔ እና መከላከያ መንገዶችን በተመለከተ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ ኢብራሂም ገልፀዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው