የሀገር ውስጥ ዜና

ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን ሙሉ ለሙሉ በባለሀብቶች ማስያዝ እንደሚገባ ተገለፀ

By Feven Bishaw

July 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በባለሀብቶች ማስያዝ እንደሚገባ እና ስራውም ለነገ የሚተው ጉዳይ እንዳልሆነ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለፁ።

የፓርኩን የስራ እንቅስቃሴ የጎበኙት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ የፓርኩ በባለሀብቶች የመያዝ ምጣኔ ለማሳደግ በዓለም አቀፍና በሀገር በቀል አምራች ኩባንያዎች ለማስያዝ ጠንካራ የፕሮሞሽን እና የማርኬቲንግ ስትራቴጂዎች ተቀርፀው በቅርቡ ተግባራዊ እንዲደረጉ አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ እንደ ሀገር የሚጠበቅበትን ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እንዲሰራ ማሳሰባቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላታል፡፡

ዶ/ር ፍሰሀ÷ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኙ የፋርማሲዩቲካል አምራች ኩባንያዎችን የምርት ሂደት በመመልከት ከኩባንያዎቹ የስራ ሀላፊዎች ጋር ውይይትም አድርገዋል።

በጉብኝት መርሃ ግብሩ የፓርኩ የ2016 በጀት ዓመት የ11 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን÷ በቀጣይ 100 ቀናት በትኩረት መከናወን የሚገባቸው ዋና ዋና ግብ ተኮር ተግባራት ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል።