አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት 426 ሺህ 290 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 600 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ ነው 426 ሺህ 290 ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለው፡፡
አፈጻጸሙ ከ2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ75 ሺህ 729 ወይም የ22 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡
የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከሆኑት አዲስ ደንበኞች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የድህረ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆኑ÷ቀሪዎቹ ደግሞ የቅድመ ክፍያ ደንበኞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የፀጥታ ችግር፣ የሲስተም መዘግየት፣ የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የዋጋ ግምትና የዋጋ ማሻሻያ ክፍያውን ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆን አፈጻጸሙ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ያደረጉ ተግዳሮቶች ናቸው ተብሏል፡፡