የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ

By Melaku Gedif

July 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የወባ በሽታ አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራትን እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።

ክልሉ የወባ በሽታ ስርጭትን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የኬሚካልና የመድኃኒት ድጋፍ ከጤና ሚኒስቴር ማግኘቱም ተጠቁሟል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ የወባ በሽታ መቆጣጠርና ማስወገድ አስተባባሪ ተወካይ አቶ ገብረመድህን ክንፉ እንዳሉት÷ በክልሉ ለ3 ተከታታይ ዓመታት አገልግሎት የሚሰጡ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ አጎበሮች ተሰራጭተዋል።

እንዲሁም ጤና ሚኒስቴር የወባ በሽታ በስፋት ሊከሰትባቸው ለሚችሉ 6 ወረዳዎች የሚውል መድኃኒትና የሚረጭ ኬሚካል ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኬሚካል ርጭት ለሚያካሄዱ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቶ ስራውን ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለህብረተሰቡ ስለ ወባ በሽታ መከላከያዎች አስቀድሞ እንዲያውቅ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል።

በመኝታ ወቅትም አጎበር የመጠቀም ልምድን ማዳበርና ኬሚካል ርጭት የተደረገባቸው ግድግዳዎችን ቀለምም ሆነ ሌላ ነገር እንዳይቀቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መካሄዱን አብራርተዋል።

የወባ በሽታ ምልክቶች የሚታይባቸው ሰዎች በወቅቱ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግና መድኃኒት ሲታዘዝላቸውም በአግባቡ መውሰድ እንዳለባቸው አስረድተዋል።