አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 4ኛው የባለልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበርና ከአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ጋር በመተባባር ውድድሩን እንዳዘጋጀው ተገልጿል፡፡
በውድድሩ እያንዳንዳቸው ከ20 ሄክታር በታች ያላቸው ከ800 በላይ የቡና አርሶ አደሮች ላለፉት 6 ወራት መወዳደራቸውና ከእነዚህም ውስጥ 150ዎቹ ለሀገር አቀፍ ውድድር ማለፋቸው ተገልጿል።
የተወዳዳሪዎች ናሙና ከጅማ፣ ሃዋሳ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ መሰብሰቡም ተጠቁሟል።
ዛሬ በተካሄደው የባለልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር 40 አርሶ አደሮች የተቀመጠላቸውን መስፈርት በመሟላት ለዓለም አቀፍ የዘርፉ ውድድር ማለፋቸው ተጠቁሟል።
ምርጥ 40 ተወዳዳሪዎቹ 12 ዓለም አቀፍ ገዢዎች በተገኙበት እንደተለዩና የውድድሩ አሸናፊዎች ነሐሴ መጨረሻ በበይነ መረብ በሚወጣ የቡና ጨረታ ምርታቸውን በከፍተኛ ዋጋ እንደሚሸጡና ላመጡትም ውጤት ሽልማት እንደሚሰጣቸው ተጠቁሟል።
በ4ኛው የባለልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር ባሻ በቀለ፣ ማቲዎስ ለሜሳና ቡኩቶ ዱሬ ከአንደኛ አስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በቅደምተከተል ይዘው እንዳጠናቀቁ ኢዜአ ዘግቧል፡፡