የሀገር ውስጥ ዜና

ሉዊስ ናኒ እና ንዋንኩ ካኑ ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያዩ

By Melaku Gedif

July 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሉዊስ ናኒ እና ንዋንኩ ካኑ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ከውይይቱ በኋላም ሉዊስ ናኒ ከሀገሩ ፖርቹጋል ማሊያ ላይ ፊርማውን አኑሮ ለፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በስጦታ አበርክቷል።

በሌላ በኩል ፖርቹጋላዊው ሉዊስ ናኒ ታሪካዊውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና 5 ኪሎ የሚገኘውን ብሔራዊ ሙዝዬም ጎብኝቷል።

በተመሳሳይ ሉዊስ ናኒ እና ንዋንኩ ካኑ የኢትዮጵያ የአየር ክልል አስተማማኝ ዘብ በሆነው በኢፌዴሪ አየር ሃይል ጉብኝት አካሂደዋል።

በኢትዮጵያ አየር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ ሲደርሱ የአየር ሃይል አዛዥ ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሁለቱ የዓለማችን ተወዳጅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አየር ሃይልን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

በካሄዱት ጉብኝት ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁት ካኑ እና ናኒ÷ ጉብኝቱ የኢትዮጵያን ታሪክና ማንነት ለመገንዘብ እንደረዳቸው ተናግረዋል።

በጉብኝት መዳረሻቸው ሁሉ ህዝቡ ላሳያቸው ፍቅርና ለሰጣቸው ክብር ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብም የዳበረ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እንዳለው መገንዘባቸውን አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሀገር ከመጠበቅ ተልዕኮው ባሻገር ለግቢ ውብትና ለግብርና ሥራዎች ልማት የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑንም ገልፀዋል።