የሀገር ውስጥ ዜና

ከፋና ጋር መስራታችን ለተቋማችን የለውጥ ጉዞ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው – ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ

By ዮሐንስ ደርበው

July 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ራሱን በዘመኑ ቴክኖሎጅ ካዘመነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በመሥራታችን ለተቋማችን የለውጥ ጉዞ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ሲሉ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ገለጹ፡፡

የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና መሥሪያ ቤት ምልከታ አድርዋል፡፡

በወቅቱ ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ፤ ኤፍ ቢ ሲ ለሕዝቡ መረጃን ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ አንድነትን ሊያመጣ በሚችል መልኩ የራሱን ቀለም ይዞ በዲጂታል ሚዲያ፣ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ አድማሱን አስፍቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከኤፍ ቢ ሲ ጋር ማረሚያ ቴሌቪዥን የተሰኘ ሳምንታዊ ፕሮግራም እያቀረበ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም ለተቋማችን የለውጥ ጉዞ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው÷ ኮሚሽኑ የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የሚያገኙትን ትምህርትና ስልጠና፣ የማረምና ማነፅ ሂደት ለሕብረተሰቡ ተደራሸ ማድረግን አስቦ ከእኛ ጋር ውጤታማ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።

የተቋማቱ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡

የኤፍ ቢ ሲ እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኃላፊዎች በ2017 በጀት ዓመት ሣምንታዊ ማረሚያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም በጋራ በሚሠሩበት ጉዳይ ላይ ስምምነት ፈርመዋል፡፡