የሀገር ውስጥ ዜና

የንግድ ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ያደረገ ማሻሻያ ስራ ላይ መዋሉ ሀገራዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው ተባለ

By Feven Bishaw

July 18, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩት የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ዘርፎች ክፍት ያደረገ የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ደንብ ስራ ላይ መዋሉ ንግድን በውድድር እንዲመራ በማድረግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው ተባለ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ግምገማ መድረክ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

“ንግድን ማሳለጥ፣ ዘላቂ እድገትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው መድረክ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ የንግድ ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ የድርሻውን በሚፈለገው መጠን እንዲጫወት ያሉበትን ተግዳሮቶች በመለየት ዘርፉን ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ወቅቱን የሚዋጁ የፖሊሲ አማራጮችን ከመጠቀም ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በሚፈለገው ፍጥነት ማሳካት የሚያስችሉ ሕጎችና መመሪያዎችን የማሻሻል ሥራዎች ተሠርተዋል፣ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችም ተመዝግበዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውንም ገልፀዋል፡፡

በዚህም ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩትን የንግድ ዘርፎች ክፍት ያደረገ የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ደንብ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ መዋሉንም አስታውሰዋል፡፡

ይህም ንግድን በውድድር እንዲመራ በማድረግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን በተሻለ መልኩ ማሳደግ ከማስቻሉም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያሉ እውቀቶችን፤ ክህሎቶችን እና ሥርዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንደ መልካም አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል።

ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ፣ ቀጣይነት ያለው እና ሁሉን አቀፍ የግብይት ስርዓትን ለማስፈን በጋራ መስራት ያስፈልገናል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ፈጠራን በመቀበል፣ ትብብርን በማጎልበት እና የዜጎቻችንን ፍላጎት በማስቀደም የበለጠ የበለጸገች እና ፍትሃዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን በማለት አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በየአካባቢው የተደራጁት 1 ሺህ 66 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘትና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ለሸማቹ ማህበረሰብ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የገበያዎችን ቁጥር ከማስፋት ጎን ለጎን የማዘመን ሥራ እየተሠራ መሆኑ ጠቁመው፤ የግብይት ማዕከላቱ ለህገ-ወጦችና ደላላዎች እንዳይጋለጡ እና ከተፈቀዱ ምርቶች ውጪ ግብይት እንዳይፈፀምባቸው የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡