አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና የህዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) ጋር የ86 ነጥብ 18 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡
የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከዩኒሴፍ ም/ተወካይ ሪኮ ካጎሺማ እና ከዩኤንኤፍ ፒ ኤ ም.ተወካይ ታይዎ ኦሉዮሚ ጋር ተፈራርመዋል፡፡
ድጋፍ በ2017 የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረጉ ሀገር አቀፍ መርሐ ግብሮችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 70 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላሩ ከዩኒሴፍ የተገኘ ሲሆን÷የተመጣጠነ ምግብ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የህጻናት ጥበቃ እና የሥርዓተ-ጾታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡
16 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ከዩኤንኤፍፒኤ የተገኘ ሲሆነ÷ለቤተሰብ ምጣኔ፣ ለእናቶች ጤና፣ ለወጣቶች ልማትና የሥርዓተ-ኦጾታ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም እንደሚውል መጠቀሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡