የሀገር ውስጥ ዜና

አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በብዙ መስኮች ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለፀች

By Feven Bishaw

July 19, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና አየርላንድ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን 30ኛ ዓመት አክብረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭና የመከላከያ ሚኒስትር ሚሼል ማርቲን እና ልዑካን ቡድናቸው ንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘላቂ ወዳጅነት ጠቅሰው÷ በቀጣይም ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፍጠር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።

እንደ አጋር በአስቸጋሪ ጊዜያት በአንድነት ቆመናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ አየርላንድ ለኢትዮጵያ ላረገችው ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስግነዋል።

የአየርላንድ ኤምባሲ በምርታማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም (ፒኤስኤንፒ) በኩል ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች በተለይም ለህጻናት፣ ለሴቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ለሚያደርገው ድጋፍ እውቅናና ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም በልማት፣ ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት፣ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና የአካባቢን ዘላቂነት ላይ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ጠንካራ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል።

ከልማት ትብብር ባሻገር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በትብብር ለመስራት ያለው አቅም ትልቅ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህንን አጋርነት የበለጠ ለማራዘም የሁለቱን ሀገራት ቁርጠኝነት ይጠይቃልም ብለዋል።

ወደፊትም ሁለቱም ሀገራት በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎችን ለማመቻቸት አየርላንድ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ሚሼል ማርቲን በኩላቸው÷ በንግድ፣ በአቪየሽን፣ በቱሪዝም፣ ለችግር ተጋላጭ ዜጎችን በመደገፍ እና በሌሎችም መስኮች የሁለትዮሸ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።