አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት የመኸር አምራችና የክረምት ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው የተስፋፋ የእርጥበት ሁኔታ ለግብርና ሥራ ተስማሚ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የመኸር የእርሻ ሥራ ዘግይተው ለሚጀምሩ አካባቢዎች የአፈር ውስጥ እርጥበትን እንደሚያሻሽልና የመኸር ሰብሎችን በወቅቱ ለመዝራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ነው የተመላከተው፡፡
ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት መሟላት እና በአሁኑ ጊዜ እርጥበት እያገኙ ላሉ በምስራቅ እና በሰሜን ምስራቅ ለሚገኙ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ ቦታዎች እርጥበቱ ከመጠን በላይ ሊሆን ስለሚችል በዚህም ምክንያት ውኃ ማሳ ላይ እንዳይተኛ የመከላከል ስራ በመስራት እንዲሁም አረምን በወቅቱ በማረም፣ ፀረ-አረምና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን በወቅቱ ከግብርና ባለሙያ በሚያገኙት ምክረ ሐሳብ በመደገፍ የማደበሪያና ጸረ-ተባይ ኬሚካሎችን አጠቃቀም የዝናቡን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ማከናዎን እንደሚስፈልግ ኢንስቲትዩቱ መክሯል፡፡
እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት መከሰት በተለይም በተከታታይ ዝናብ እያገኙ ባሉ ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው ቦታዎች አርሶ አደሩ እና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሆን በሰብሎች፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው የተባለው፡፡