የሀገር ውስጥ ዜና

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውጤታማ ስራዎችና ተሞክሮዎች ተመዝግበዋል ተባለ

By Shambel Mihret

July 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ ውጤታማ ስራዎችና ተሞክሮዎች መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

የክልሉ የ2016 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግስት ስራዎች ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

በዚሁ ወቅት አቶ እንዳሻው ጣሰው÷ ክልሉ በአዲስ መልክ ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 11 ወራት በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችና ተሞክሮዎች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

ስራዎችን በየጊዜው በመገምገምና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡

መድረኩ የተገኙ የልማት ተሞክሮችን በማስፋትና ጉድለቶችን በማረም በተያዘው በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ አቅጣጫ የሚቀመጥበት እንደሆነም ተናግረዋል።

መድረኩ የበጀት አመቱን ስራዎች አፈጻጸም በመገምገም የ2017 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎችና ክልላዊ ግቦች ያስቀምጣል መባሉንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡